ቤትዎ ቁጭ ብለው የሚሰሩት ስራ መጣልዎ! እንዴት ከታች ምስሉን ተጫኑ

Sunday 11 November 2018

የትንሹ ሊዮኔል ሜሲ ህልም እና "ፒቤ" ታሪክ (መንሱር አብዱልቀኒ)


በዚያች ምሽት ሊዮ ሰማያዊውን ኳስ በአልጋ ውስጥ ሸሽጎ ጋደም አለ። አባት ሆርጌ ወደ መኝታ ክፍሉ ሲገባ እንዳላየ ሆኖ በአልጋው ላይ፣ ከልጁ ጎን ተቀመጠ።

"ግን አቧራውን ጠርገኸዋል?"

"አዎ አባዬ!" ... ሊዮ ኳሱን ደበቅ በማድረግ፣ ፈጠን ብሎ
የተለደፈበትን ቀይ ጭቃ ጠራረገ። ኳሱ ለልደት ስጦታ ከተበረከተለት አንድ ዓመት ሆኖታል። በሮዛሪዮ አቧራማ መንደሮች ላይ ሲለፋ ቆይቶ፣ የአዲስነት ገፅታውን አጥቷል። ተቦጫጭሯል፣ ተፋፍቋል። የሊዮ ምርጡ ጓደኛ ቆሽሾም ቢሆን ማታ አብሮት ይተኛል።

"ፀሎት አድርሰሃል?" አባት ጠየቀ።

"አዎን አባዬ! ፈጣሪ ቁመቴን እንዲያረዝምልኝ ጠይቄዋለሁ!" ሊዮ መለሰ። ገና ከጨቅላነቱ በኳስ ፍቅር የተለከፈው ታዳጊ ጭንቀት የተሰጥኦ ሳይሆን የተክለ ሰውነት ነበር። ፀሎቱም አምላክ የሌለውን እንዲሰጠው የሚማፀንበት ሆኗል።

ትንሹ ልጅ የቁመቱ ነገር እንዲህ ሲያስጨንቀው ማየት የአባትን ልብ የሚሰብር ነበር። በጎንዮሽ ተመልክቶት አዘነ። የጥፋተኝነት ስሜት አስጨነቀው። ለዚህ ተፈጥሯዊ ችግር መፍትሔ ለማግኘት አባት ከሚችለውም በላይ ቢሆን ጥረት ማድረግ እንዳለበት አመነ።

"የፒቤን ታሪክ ጓደኞችህ አውርተውልህ ያውቃሉ? ሲያወሩ ሰምተህ ታውቃለህ?"

"ፒቤ?... ፒቤ ምንድነው?" ሊዮ የአባቱን ጥያቄ በጥያቄ መለሰ።

"ፒቤ ማለት እግር ኳስን በሰፈር ጎዳናዎች ላይ በመጫወት ያደገ፣ ልዩ ተሰጥኦን የታደለ አርጀንቲናዊ ልጅ ማለት ሲሆን በብቃት ድሪብል ማድረግ የሚችሉት ብቻ የሚጠሩበት ስያሜ ነው።"

"እንደ ማራዶና አይነቱ?"

"አዎን! ልክ እንደ ማራዶና ማለት ነው። ማራዶና የዘመናችን ፒቤ ነው።"

"እና ታሪኩ የማራዶና ነው?"... የታዳጊው ሊዮ ጥያቄ ቀጠለ።

ሆርጌ ረጋ ብሎ መልስ ሰጠው።

"አይ! አይደለም ልጄ! ታሪኩ የማራዶና ሳይሆን ያንተ ነው"

ሊዮ እጅግ ተደሰተ። ሲያድግ ፕሮፌሽናል ተጫዋች መሆንና በማራዶና ስር መሰልጠን ምኞቱ ነበርና የአባቱ ወሬ አበረታው። ብሩህ ተስፋ አሳየው። ሆርጌ ታሪኩን እየተረከለት፣ ሊዮም እያደመጠ ወደ አባቱ ዞሮ ፈገግ እንዳለ፣ እንደተደሰተ እንቅልፍ አሸንፎት፣ አሸለበ።

…የዚያች ሌሊት ህልም፣ ተራ ህልም አልነበረም። በዚህ ዘመን እየሆነ ያለውን ሁሉ ቀድሞ፣ በለጋ ዕድሜው አርቆ ያየበት የእንቅልፍ ዓለም መነፅር ነበር!
                             
                                * * *

... ሊዮኔል ሜሲ ገና የአምስት ዓመት ታዳጊ ነበር። በሮዛሪዮ ከተማ፣ በ525 ኤስታዶ ደ ኢስራኤል ጎዳና በሚገኘው የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ጀርባ በሚገኘው ትንሽ ሜዳ ላይ  ኳስ በመጫወት ላይ ሳለ ወደ ጎሉ በድንገት ሲመለከት በሁለቱ የእንጨት ቋሚዎች መካከል ዲዬጎ ማራዶና ቆሞ አገኘው። ጥቁር ማሊያ ለብሶ በበረኛነት ግቡን ይጠብቃል።

ማራዶናን ሲመለከት ሊዮ በድንጋጤ ቆመ። ይህን ሲያይ፣ ዲዬጎ ይጮህበት ጀመር። "ሊዮ እንዳትቆም፣ ቀጥል! ቀጥል! ምታ!  ጨዋታው ያንተው ነው ፒቤ!"

ሊዮ ኳሷን ወደ ፊት በቄንጥ ገፋ አደረጋት፣ ወደ ቀኝ አጠፋት፣ ከዚያ በግራ እግሩ ጠበቅ አድርጎ በዲዬጎ ግራ በኩል ላካት። በማራዶና አናት ላይ ተንሳፋ፣ በግቡ አግዳሚ እንጨት ስር አልፋ ከመረቡ ጋር ተገናኘች።

ሊዮ እጁን ወደ አየሩ ዘርግቶ፣ በድል አድራጊነት ስሜት ወደ ማራዶና ተመለከተ። ሙከራውን ማዳን ባለመቻሉ በብስጭት የጦፈ ሰው ሲጠብቅ ያልገመተው ሆኖ ተገኘ። ዲዬጎ ደስተኛና ሳቂታ ሆኖ ያበረታታው ጀመር።

"አበጀህ! ሊዮ! ...ምትሃታዊ ነበር! አበጀህ!... ላ ኑኤስተራ!"

ዲዬጎ ተደስቶበት ሜሲን በሁለት እጆቹ  አንከብክቦ፣ እንደ ሳንቲም ወደ ላይ ወረወረው። ትንሹ ልጅ ወደ መሬት ከመውረድ ይልቅ በአየር ላይ ተንሳፈፈ። ቁልቁል ቢመለከት ማራዶና እያነሰ፣ እያነሰ ሄደ። ዲዬጎም ለመጨረሻ ጊዜ ጮክ ብሎ ነገረው።

"ሊዮ...! በእውነት አንተ ፒቤ ነህ!..."

ማራዶና ይህን ሲናገር ሜሲ በላዩ ላይ የተከመረው ፍርሃት ጥሎት ሲሸሽ ተሰማው። ወደ መሬት ሳይመለስ ዲዬጎን እንዲህ አለው።

"ፒቤው አንተ መስለኸኝ ነበርኮ!"

የማራዶና ድምፅ በደመናው ውስጥ እያስተጋባ ምላሹ ተሰማው።

"አዎን ሊዮ!... እኔ ፒቤ ነኝ። አንተ ደግሞ ቀጣዩ ፒቤ ትሆናለህ!"

ሊዮ ያየውን ማመን አልቻለም። አሁንም ተንሳፏል። ወደ ላይ ከፍታው ጨምሯል። ውሃ ውስጥ ያለ ይመስል፣ በመታጠቢያ ቤት ገንዳ ውስጥ እያስመሰለ እንደ ዋናተኛ እንደሚጫወት ሁሉ፣ በደመናው መካከል ይዋኛል። ቀና ሲል አይኖቹ የፀሐይዋን ነፀብራቅ ሊቋቋሙ አልቻሉም። የጨረሩ ድምቀት ከእንቅልፉ አነቃው።

ከህልም ዓለም ሲመለስ…፣ ራሱን በአልጋው ላይ፣ በአልጋ ልብሱ መካከል በደረቁ ሲዋኝ አገኘው። አቅፎ የተኛት ሰማያዊዋ ኳስ ከአልጋው ተሽቀንጥራ ወርዳ፣ በክፍሉ ወለል ላይ፣ መስኮቱ ስር ቆማ አገኛት።

ነግቷል።

"ይገርማል! ይገርማል!"... እያለ ሊዮ በመገረም፣ ከአልጋው ተነሳ። ለብቻው ያወራ ነበር።

"ምኑ ነው የሚገርመው?" አያቱ ሴሊያ መልስ ሰጡት።

"አያቴ፣ ከእስካሁኑ ሁሉ ምርጡን ህልም አየሁ።"

"እሺ! በቃ! ወደ ግራንዶሊ እየሄድን ምን እንዳለምክ ትነግረኛለህ!"

"ግራንዶሊ? እዚያ ምን እንሰራለን? ጨዋታ ልናይ?"... አለ ሜሲ፣ የአልጋ ልብሱን አንስቶ ወደ አያቱ አናት አቅጣጫ በመወርወር።

"እንዴ! ሄደህ ጨዋታ ማየት ብቻ ነው የምትፈልገው?" ሴሊያ በአናታቸው ላይ የተከመረውን ጨርቅ በማውረድ፣ ፀጉራቸውን እያስተካከሉ ጠየቁት።

"አይ! መጫወትም እፈልጋለሁ እንጂ!"

ሜሲ በዚያች ጠዋት ግራንዶሊ ለተባለው የህፃናት ቡድን ተመዝግቦ ለመጫወት ይሞክር ዘንድ አያቱ ወደ ቦታው ሊወስዱት አስበዋል....።

                              * * *

(የሊዮ ሜሲ አስደናቂው ህይወት ከሚለው የማይክል ፓርት መፅሐፍ ተወስዶ በአጭሩ ለመፃፍ እንዲመች ተብሎ የቀረበ)
                               * * *
(ምንጭ፦ መንሱር አብዱልቀኒ ፌስቡክ ገፅ)

No comments:

Post a Comment