ቤትዎ ቁጭ ብለው የሚሰሩት ስራ መጣልዎ! እንዴት ከታች ምስሉን ተጫኑ

Friday 16 November 2018

ፖል ስኮልስ ያ ምሽት፣ ያ ማሊያ (የአሸናፊውና ተሸናፊው ወግ)



(በመንሱር አብዱልቀኒ)
"ስለዚያ የፍፃሜ ጨዋታ ሳስብ፣ የሚታወሰኝ የመጨረሻው 30 ደቂቃ ነበር" ይላል ኤሪክ አቢዳል። ስለ2011ዱ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ እያወራ ነው። ገና ሊጠናቀቅ ግማሽ ሰዓት እየቀረው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ። የባርሴሎናን የምሽቱን ኃያልነት ምንም አይነት ጥረት ሊቀለብሰው እንደማይችል ዩናይትዶች ቀድመው ተረዱ። እንደው ቦክስ አይደል ፎጣ አይወረወር ነገር!

የባርሳ ልጆች ይጫወቱታል። በእግሮቻቸው ቅብብል ሜዳውን በአይነ ህሊናዊ መስመሮች ይሸረካክቱታል፣ ያለ እጅ ንክኪ ይከፋፍሉታል፣ ያለ ቢላዋ ይበልቱታል። እኒያ ታላቅ ጀግና ሰር አሌክው ፈርጉሰን እንኳን ዓይኖቻቸው በካታላኑ ጥበባዊ ትርምስ ቦዘው ስልት የተሟጠጠበት የጦር መሪ መስለዋል።

ኢኒዬሽታ ለቻቪ…፣ ቻቪ ለሜሲ ይሰጠዋል።… ከዚያ ቡስኬትስ ይመጣና ይቀበላል፣ መልሶ ያቀብላል። ፒም-ፓም…፣ ፒም-ፓም…፣ ፒም-ፓም…።

"እንግሊዛዊያኑ ተጫዋቾች ተማረሩ" አቢዳል ስለመጨረሻው 30 ደቂቃ ትውስታውን ቀጠለ።

"ዌምብሌይን ወደ ግዙፍ ሮንዶ (መሐል ባልገባ) ስለቀየርንባቸው ብስጭት ገባቸው። ሊያቆሙን አቃታቸው። አቅመ ቢስ ሆኑ።

"የብልግና ቃላትን ጨማምረው የብስጭታቸውን ያህል ይናገራሉ። ምን ቀራቸው…፣ ከፀሃይ በታች ባለ ስድብ ሁሉ ይጮሃሉ። ይገርማል። ከቡድን ጓደኞቼ አንዳንዶቹ ተጫዋቾቹ በቋንቋ ምክንያት ምን እያሉ እንደሆነ አልገባቸውም ነበር። እኔ ግን ተረድቼዋለሁ። "…በቃኮ! አልቆልናል፣ ሞተናልኮ። በቃ! ለምን አይበቃችሁም?" ሲሉን ጨዋታው ሊያልቅ ገና 25 ደቂቃ ይቀረው ነበር።

ቻቪ፣ ኢኒዬሽታ፣ ቡስኬትስ ቀጠሉ። ፒም-ፓም…፣ ፒም-ፓም…፣ ፒም-ፓም…።

አቢዳል እንከን የለሽ የቡድን ስራ፣ ወደ ውብ ጨዋታ ሲቀየር እያስተዋለና ራሱም እየተጫወተ ነበር። በህልም ዓለም የሚታሰበው ሁሉ እየሆነ ነው። ለእርሱ ልዩ፣ ከልዩም ልዩ ጨዋታ ነበር።

አቢዳል በመጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ ይካተታል ብሎ የገመተ አልነበረም። በጉበቱ ላይ የካንሰር ዕጢ መገኘቱ ከተነገረ ገና ሁለት ወር መሆኑ ነው። መጥፎው ዜና በተሰማ ማግስት ከጨዋታ በፊት መልበሻ ቤት ገብቶ ጓደኞቹን አበረታቷል። ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ቀዶ ጥገናው ክፍል ሲገባ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ለተጨዋች ጓደኞቹ "ጉበቱን የሚሰጠኝ" እያለ ይቀልድባቸው ነበር። ሜይ 28 ደግሞ በዌምብሌይ ለፍፃሜው ተሰለፈ።

"ልዩ የሆነብኝ ፑዮልና ቻቪ ዋንጫውን እንዳነሳ ዕድል ስለሰጡኝ ወይም በዌምብሌይ የሞቀ ድባብ ምክንያት እንዳይመስላችሁ። በፉትቦሉ ጥራት እንጂ…" ይላል።

ያኔ አንድሬስ ኢኒዬሽታ በችሎታው ተራራ ጫፍ ላይ ነበር። ዌምብሌይ ከጉዳት ነፃ የሆነበት የመጀመሪያው የፍጻሜ ጨዋታ ሆነለት። እንደ እምቦሳ እየፈነጠዘ፣ እንደ ልባም ፈረስ እየጎደፈረ፣ ኳሷን በተዓምራዊ ፍጥነትና ጥበብ ወደፈለገው ቦታ እየላካት ያዛታል።

የኦርኬስትራው አካል ቢሆንም አቢዳል ተመልካችም ጭምር ነበር። ካታላኑ በኳስ ቅብብል ያለድምፅ ያዜማሉ። ጥበብ በኢኒዬሽታ ያማረ መልኳን ስትገልጥ ፈረንሳዊው ተከላካይ እየታዘበ ይደመማል።

ቻቪ የአቢዳልን ትውስታ ያጠናክራል።

"…አዎን! አቢ እውነቱን ነው። ሩኒ ወደ እኔ መጣና አነጋገረኝ። 'አይበቃችሁም እንዴ? በቃ አሸንፋችኋልኮ' አለኝ። ሰዓቱ ግን 80ኛ ደቂቃ ገደማ ነበር። 'በቃ ኳሱን ማንሸራሸራችሁ ይብቃ  ' ይለኝ ነበር።…"

አያልቅ የለ የፍፃሜው ፊሽካ ተሰማ። ፔፕ ጋርዲዮላና ልጆቹ አሳምነው 3ለ1 አሸነፉ። ባርሳ የአውሮፓ ሻምፒዮን ተባለ።

ካርለስ ፑዮል የአምበልነቱን ጥብጣብ በፍቃደኝነት በአቢዳል ክንድ ላይ አሰረው። ከካንሰር ህመም በህክምና ጥበብ የተመለሰው አቢ ዋንጫውን በክብር ሲያነሳ ስኮልስ ባለ 18 ቁጥሩ ነጭና ቀዩን ማሊያ ለብሶ ትዕይንቱን ፈዞ ይመለከታል። በእውነት ይህን ያህል ተበልጠን እንሸነፋለን ብሎ አልገመተም ነበር።

በዚያች ምሽት፣ በለንደን የእግር ኳስ ካቴድራል ተሸናፊው ሰራዊት ዩናይትድ ቢሆንም፣ የድል አድራጊዎቹን ልብ ቀድሞ በአድናቆት ያቀለጠ ተጫዋች ከዚያ ወገን ውስጥ አለ። የባርሳ ከዋክብት ከፖል ስኮልስ ጋር መጫወትን ሲመኙ ኖረዋል። ቻቪ እጅጉን ያደንቀዋል፣ ኢኒዬሽታ "ምነው ከእርሱ ጋር በአንድ ቡድን ውስጥ ባጫወተኝ" እያለ አልሟል።

የእርሱን ማሊያ "እኔ እወስድ፣ እኔ እወስድ" እያሉ ሲጨቃጨቁበት አቢዳል ሰምቷል። በዚያ ምሽት አድናቂዎቹ በድል ደስታ ሰክረው ሳለ ስኮልስ ግን ከእነ ማሊያው ቆሞ የሽንፈቱን ራስ ምታት ያዳምጥ ነበር።

ተሸናፊው የአሸናፊዎቹን ፓርቲ እየታዘበ የዌምብሌይ ሜዳ አልበቃህ ብሎት፣ በእግሩ የነካው ሁሉ ወርቅ ሲሆንለት ያየው አንድሬስ ወደ እርሱ መጥቶ ማሊያውን ሲጠይቀው ሳይደነቅ አልቀረም።
                             
… ኢኒዬሽታ በተወለደበት ፎንቴያልቢያ የወይን እርሻ ባለቤት ነው። ከእርሻውም ጎን የወይን ጠጅ መጥመቂያ ፋብሪካ አለው። እዚያው መኖሪያ ቤቱን ገንብቷል። ከቤቱ ጓዳዎች በአንዱ፣ በወይን ጠጅ ማከማቻ ክፍል ግድግዳ ላይ በመስተዋት ፍሬም ውስጥ አንድ ብርቅዬ ማሊያ በክብር ተሰቅሏል። ፖል ስኮልስ በዌምብሌይዋ ምሽት የለበሰው ያ ማሊያ።

(ምንጭ፦ መንሱር አብዱልቀኒ Facebook ገፅ)
ምስል ቅንብር እና አዘጋጅ - መንግስቱ ደሳለኝ

No comments:

Post a Comment