ቤትዎ ቁጭ ብለው የሚሰሩት ስራ መጣልዎ! እንዴት ከታች ምስሉን ተጫኑ

Thursday 15 November 2018

Moments: ጆዜ ሞሪንዎ ያቺን ሰአት (በመንሱር አብዱልቀኒ)

ሞውሪንሆ ያቺን ሰዓት

በሪያል ማድሪድ መልበሻ ቤት የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ አለ። ጆዜ ሞውሪንሆ አድብቶ የሚያስጠቃቸውን የዚህን ፍልፈል ማንነት አላወቁም። ዕረፍት ነሳቸው። የመልበሻ ክፍሉን ድብቅ መረጃዎች ለጋዜጦች የሚሰጠው ማነው? ጆዜ ቆረጡ። "መጋለጥ አለበት" አሉ።

የጋዜጦችን ዕለታዊ ወሬ ሰብስበው በየማለዳው ጠረጴዛቸው ላይ የሚያስቀምጡላቸውን ሰዎች በወኪላቸው ዦርጌ ሜንዴዝ ኩባንያ "ጄስቲፊዩት" በኩል ቀጠሩ። ሰዎቹ ሚድያ የተነፈሰውን ሁሉ… እንደወረደም ይሁን ተብራርቶና ተተንትኖ ለአለቃቸው ያቀርባሉ።

የጆዜ ቀን ዘወትር ከማለዳው 2:00 ሰዓት ላይ ይጀምራል። በልምምድ ማዕከሉ በሚገኘው ቢሯቸው የጋዜጣ ላይ ዘገባዎችን፣ አስተያየቶችንና የቲቪ ፊልሞችን በማየት አይናቸውን ይገልጣሉ። ሚድያው የቡድኑን ምስጢር ሁሉ ይዞ መውጣቱን ቀጥሏል። ጆዜ አንጀታቸው እያረረ መልስ ያላገኙለትን ጥያቄ ይጠይቃሉ። ፍልፈሉ ማነው?

የመረጃውን ጥራት ሲመለከቱት ደግሞ በቡድኑ አባላት መካከል ባሉ ሰዎች በኩል የሚወጣ ምስጢር አልመስልህ አላቸው። የሆነ…፣ የተደበቀ ድምፅ መቅጃ ሳይኖር እንደማይቀር ጠረጠሩ። በድብቅ ንግግሮቻቸውን የሚያደምጥ ካልሆነ በስተቀር ያቦኩት ሳይጋገር ለአደባባይ ሊበቃ አይችልም።

ቡድኑ ከጨዋታ በፊት በሚያርፍበት ሆቴል ውስጥ የሚሰሩ ሁለት የፅዳት ሰራተኞች ድብቅ መቅረፀ ድምፅ እንዲፈልጉ አዘዟቸው። ሼራተን ሚራሲዬራ ተበረበረ፣ በየጥጋጥጉ ተፈተሸ። ምንም አልተገኘም።

ጆዜ ጦፉ። ቀጣዩ ጨዋታ ኤልክላሲኮ ስለሆነ ደም፣ ደም ሸቷቸዋል። ሲብስባቸው ለክለቡ ከፍተኛ አለቆች የተጫዋቾቻቸውንና ሰራተኞቻቸውን የስልክ ምልልስ እንዲጠልፉና የሚያወሩትን እንዲቆጣጠሩ ጠየቋቸው። አንዳንድ ተጫዋቾች ነገሩ በማስጠንቀቂያ መልክ ተነገራቸው። በእጅ ስልኮቻቸው በኩል የሚያወሩትን ነገር ይዘትና የሚያነጋግሩትን ሰው ማንነት እንዲመርጡ ተመከሩ።

አፕሪል 16 ቀን 2011፣ በቤርናቢዩ ከባርሳ ጋር ከመጫወታቸው ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ማርካ ጋዜጣ "ዛሬ ፔፔ ይሰለፋል፣  ኬዲራ እና አሎንሶ ያጣምሩታል" ሲል ሜሱት ኦዚል ተጠባባቂ እንደሚሆን ዘገበ። እንደገና ምስጢር አፈተለከ።

ሰዓቱ ደርሶ ቡድኑ ሊሟሟቅ ሲወጣ ተጫዋቾች በሜዳው ላይ ያልተለመደ ነገር አስተዋሉ። ሳሩ ከወትሮው ይልቅ ረዝሟል። በቅጡ አልታጨደም። ረጅምና ደረቅ ነው። የባርሳን የኳስ ሂደት ለማወክና ለማዘግየት መሆኑ ግልፅ ሆነላቸው።

በጨዋታው ማድሪድ በትዕዛዝና በኃይል መከላከልን መረጦ አፈገፈገ። ባርሳዎች ደግሞ ኳሱን አብዝተው በእግራቸው ስር አቆዩ። ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች ተሰጡና ሁለቱም ተቆጠሩ። አንድ በሮናልዶ፣ አንድ በሜሲ። የመጨረሻ ውጤት? ... 1- 1።

ከዚህ ጨዋታ በፊት ከጋርዲዮላ ባርሳ ጋር በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች 0-2 እና 2-6 ተሸንፈዋልና አሁን ባያሸንፉም የቤርናቢዩ ደጋፊዎች እፎይታን አገኙ። አቻው ውጤት ግን የሪያልን የዋንጫ እድል የሚያጠብ ነበር።

ጆዜ ተጫዋቾች በመልበሻ ቤት እስኪሰባሰቡ ጠብቀው ማንባረቅ ጀመሩ። ስድብ አዘል የስፓኒሽ ቃላት እንደ በረዶ ውሽንፍር በተጫዋቾቹ ላይ ዘነቡ።

"ከሃዲዎች ናችሁ! ከዳተኞች! የማትታመኑ ናችሁ! ስለቡድኑ አሰላለፍ ለማንም እንዳትናገሩ ነግሬያችሁ ነበር። እናንተ ግን ከእኔ ወገን እንዳልሆናችሁ አሳያችሁ። የውሻ ልጅ ሁሉ! ብቸኛው ጓደኛዬ ግራኔሮ ብቻ ነበር። አሁን ግን እርሱንም ማመን እየቸገረኝ ነው። ብቻዬን ተዋችሁኝ። ከገጠሙኝ ቡድኖች ሁሉ እንደዚህ ከዳተኞች የበዙበት ስብስብ አይቼ አላውቅም…።"

የአሰልጣኙ ቁጣ ማለቁን ሳይጠብቅ ኢኬር ካሲያስ ጥሏቸው ወደ መታጠቢያ ክፍሉ ገባ። አንዳንዶቹም ተከተሉት። ንዴት እንደ ጉሽ ጠላ አናታቸው ላይ የወጣባቸው አሰልጣኝ በአፍታ እብደት አጠገባቸው ያገኙትን ሬድ ቡል በካልቾ ጠለዙት። ቆርቆሮው በኃይል በሮ ከግድግዳው ጋር ሲላተም እግረ መንገዱን በውስጡ የያዘውን ፈሳሽ በአቅራቢያው በሚገኙ ተጫዋቾች ፊት ላይ ረጨው።

ያኔ ጆዜ በንዴት በግነውና ተጨማሪ ስድቦችን አስከትለው፣ እየተቆጡ በመልበሻ ቤቱ ወለል ላይ በጉልበቶቻቸው ተንበረከኩ። ሲነሱም በዓይናቸው ስር እምባቸውን ይጠራርጉ ነበር። ዛቻ አስከትለው ለቁጣቸው ማሳረጊያ አበጁለት።

"ግዴለም! ለ[ፍሎሬንቲኖ] ፔሬዝ እነግረዋለሁ። ራሱ ወሬ አቀባዩን ፈልጎ ያጋልጠው። በቪዬትናም ብሆን ኖሮ፣ በጓደኛችሁ ላይ እንዲህ ስትቀልዱ ብመለከት ሽጉጤን መዝዤ በደፋኋችሁ ነበር…።"

No comments:

Post a Comment